የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ የ2018 ዓ/ም የፀጥ...

image description
image description
image description
image description
image description
image description
image description
image description
image description
- recent news   

የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ የ2018 ዓ/ም የፀጥታ ጥበቃ አፈፃጸሙን በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን አስቀመጠ፡፡

የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ የ2018 ዓ/ም የፀጥታ ጥበቃ አፈፃጸሙን በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን አስቀመጠ፡፡

 ነሐሴ 07 ቀን 2018 ዓ/ም

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌ/ጀነራል አስራት ደኔሮ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በተመራው የጥምር ኃይሉ ዕቅድ ውይይት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለ ስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ም/ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዦች ም/ኮሚሽነር ቶፊቅ መደድና ም/ኮሚሽነር እርዚቅ ኢሳ፣ የሀገር መከላከያ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ አዛዦች እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ አካሉ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የጋራ ግብረ ኃይሉ ስኬታማ ስራ እንደሰራ ጠቁመው የወንጀል ስጋትን ማስቀረትን መሰረት ያደረገና የታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት እንዳይሳካ የማድረግ የተጠናከረ ቅንጅታዊ አሰራር መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል።

ወንጀልን መከላከልና ተፈፅሞም ሲገኝ የመመርመርና ህብረተሰቡን በማሳተፍ እንዲሁም መረጃን በማደራጀት የሚከናወነውን ተግባር በማጠናከር የፀረ ሠላም ሀይሎችን ተልዕኮ ወስደው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በሚገባ መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበው የተገኘውን ሠላም ለማስቀጠል መረጃዎችን መሰብሰብና ማደራጀት ተገቢ እንደሆነም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌ/ጀነራል አስራት ደኔሮ ባሳለፍነው 2018 ዓ/ም ጥምር የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በቅንጅት በመስራቱ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫን ጨምሮ በከተማዋ የተከናወኑ የተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአደባባይ ኩነቶች እና ኮንፈረንሶች በሠላም እንደተጠናቀቁ ገልፀው በቀጣይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከተማዋን ለማተራመስ የሚሞክሩ ፀረ ሠላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ መግታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከልም የጋራ ግብረ ኃይሉ ፈጣንና አሰተማማኝ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበው የኤሌክትሮኒክስ መረጃዎችን በማቀናጀት የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል።

በቀጣይም የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32 ከ80ሺ በላይ እንግዶች እንደሚሳተፉ ተናግረው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም  ጉባኤው ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው ባሳለፍነው 2018 ዓ/ም ከ7ሺ 700 በላይ ኩነቶች ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር በሠላም ሊጠናቀቅ የቻለው በቅንጅት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የፀጥታ መዋቅሩ ጠንካራ ስራ በመስራቱ መሆኑን ተናግረው ህብረተሰቡ በአካባቢው ላይ የነቃ ተሳትፎና ጥበቃ እንዲያደርግ በመደረጉ ወንጀልን በመቀነስ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱንም ገልፀዋል።

ጠንካራ ስምሪት በማድረግ የከተማዋን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የክረምት ዕቅድ ወጥቶ የወንጀል ስጋቶችን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሆነ አመላክተው በማህበረሰብ አቀፍ አደረጃጀት ከብሎክ ጀምሮ የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከል አስፈላጊው ቁጥጥርና እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በ2018 ዓ/ም በፀጥታና ደህንነት የጋራ ግበረ ኃይሉ በተከናወነው የፀጥታ ማስከበር ተግባር የተገኘውን ስኬት በማስቀጠልና ለ2019 ዓ/ም በተሰጠው ዕቅድና አቅጣጫ መሰረት ሌት ተቀን የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
*
ዘገባው የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው ፦በረ/ኢንስፔክተር ዳዊት እርገጤ
*