የአካባቢ ህዝብ ቅጥር ጥበቃ አባላት የወንጀል መከላከል አቅምን ለማሳደግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።
የአካባቢ ህዝብ ቅጥር ጥበቃ አባላት የወንጀል መከላከል አቅምን ለማሳደግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።
******
የካቲት 24/2018 ዓ.ም (ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ፤ በአካባቢ ህዝብ ቅጥር ጥበቃ አባላት ላይ ያተኮረ የወንጀል መከላከልና የስነ-ምግባር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
በተሰጠው ስልጠና ላይ የወንጀል ምንነት፣ ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል ስልቶች፣ ወንጀል በማህበረሰቡ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት፣ የወንጀል መንስኤዎችና የህግ ማስከበር ግቦች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
ስልጠናውን የሰጡት የዘርፉ ዳይሬክተር ኮማንደር ሙሉጌታ በጋሻዉ ሲሆኑ የህዝብ ቅጥር ጥበቃ አባላት የከተማዋ የጸጥታ መዋቅር ወሳኝ አካላት መሆናቸዉን አንስተዉ፤ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ መከላከል የሚቻለው አባላቱ የወንጀል መንስኤዎችን በሚገባ ሲረዱና በስነ-ምግባር የታነጸ የጥበቃ ስራ ሲያከናውኑ ነዉ ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለዉም ይህ ስልጠና አባላቱ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት አካባቢያቸውን ከስጋት ነጻ እንዲያደርጉ አቅም ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ስልጠናዉን በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል።
ስልጠናዉ የ5 ክፍለ ከተሞች የቅጥር ጥበቃ አባላትን ያሳተፈ ሲሆን፣ በቀጣይ ቀናት በቀሪዎቹ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ አባላትም ተመሳሳይ ስልጠና የሚያገኙ መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ቢሮው የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በዘላቂነት ለማረጋገጥና የጥበቃ አባላትን የሙያ ስነ-ምግባር ለማሳደግ እየሰራ ካለዉ ተግባር አንድ አካል ነው።