ለ130ኛ ጊዜ የሚከበረው የአድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት መድረክ ተካሄደ።
"እኛ ኢትዮጵያዊያን ለብሔራዊ ጥቅም መቆም ከየትም ያመጣነው ወይም የኮረጅነው ሳይሆን ለዘመናት በሕዝቦቿ ውስጥ የተፈጠረ፣የአብሮነትና የሃገር ፍቅር ውጤት ነው"።
ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ
የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አ.አ.ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
*****
ክብርት የቢሮ ኃላፊዋ ይህን ያሉት ለ130ኛ ጊዜ የሚከበረው የአድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት መድረክ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።
ኃላፊዋ በንግግራቸው ወቅትም እንደተናገሩት ይህ ድል የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚቀይር በሰላም ላይ የምትገኝ አንድነቷ የጸና እና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያነሳሳ ድል ሲሆን፣ዳግማዊ አድዋ ድል ማለትም የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ህያው ማሳያ እንደሆነው ሁሉ ለሌላው ብዙ ዳግማዊ አድዋ ተምሳሌት ስኬቶች እና ለማይቀረው ሁለንተናዊ ብልጽግና እንድንተጋ የሚያነሳሳን ታላቅ ድል ነው ብለዋል።
የዘንድሮው የ130ኛው የአድዋ ድል በዓል ለየት ያለ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምናከብረው ሲሆን በዋናነትም በይቻላል መንፈስን ሰርተን ውጤቶቻችንን እና መልካም ገፅታችንን ለዓለም አጉልተን ባሳየንበት፣የሃገራችን የወደፊት ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ሀገራዊ ትልሞችን በንጋት ሃይቅና በጉባ ተራሮች ላይ ብስራቶችን ያወጅንበት፣7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚከወንበት ጊዜ ላይ ሆነን የምናከብረው ነው ሲሉ ወ/ሮ ሊዲያ ገልጸዋል።
የግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንገባ ጽንፈኛ ቡድኖች ተደራጅተው፣ነፍጥ አንግበው፣የውስጥ ሰላማችንን ሊያደፈርሱ እየሰሩ በመሆን እና የውጭ የጠላት ሃይሎች ደግሞ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን አቅደው ስለሚንቀሳቀሱ እኩይ ተልዕኳቸውን ማምከን የከተማችንን ውስጣዊ ሰላምን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ሲሉም ተደምጠዋል።
የ130ኛ ዓመት የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ "የአድዋ አደራ አንድነት፣ሉዓላዊነትና ማንሰራራት!!"በሚል መሪ ቃል ለፀጥታ አካላት የፓናል ውይይት ሰነድ በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የሃይማኖትና የሰላም ዕሴት ግንባታ ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ በሆኑት በአቶ ብርሃኑ ረታ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
ክቡር ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ በመድረኩ ማጠቃለያ እንዳሉት የአድዋ በዓል ለኢትዮጵያን የነጻነት እና የድል በዓል መሆኑን ጠቅሰው፣የዚህ ድል ባለቤት መሆናችን ኩራት ሊሰማን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውሞ የህዳሴ ግድብ በመደጋገፍ ዳግማዊ አድዋን ማስመዝገብ እንደተቻለና የዚህ ዓመት የአድዋ ድል በዓልን ማክበር ለየት እንደሚያደረገው ጠቁመው፣በኢኮኖሚ፣በፖለቲካዊና በማህበራዊ የመላውን የህዝባችን የዘመናት ጥያቄ የቀይ ባሕር ትኩረት ሰጥተን ዳግመኛ የአድዋ ድል እንደሚሆን ታሳቢ አድርገን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞችን ስርዓት ማስያዝና የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ ክብርት የቢሮ ኃላፊዋን ጨምሮ፣ ክቡር ሌትናንት ጀነራል በላይ ስዩም፣የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ፣ክቡር ኮሚሽነር ጌቱ አርጋ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጠቅላይ አዛዥ፣ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ስራአስኪያጅ፣የመከላከያ ሚኒስቴር አመራሮችና አባላት ፣የፌደራል ፖሊስ፣የአዲስ አበባ ፖሊስ፣የደንብ ማስከበር እና የሰላምና ፀጥታ አመራሮች፣ አርበኞች፣የሰላም ሰራዊት አባላትና የቅጥር ጥበቃ አባላት ተገኝተዋል።