ቢሮው በከተማዉ በሚገኙ ከ4 ሺህ በላይ ብሎኮች ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የምዘና ተግባር ያለበትን ደረጃ የሚገመግም መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ይበልጥ ለማረጋገጥ እየተካሄደ ያለው የብሎኮች ምዘና ተግባር ተገመገመ።
*
ጥር 25/2018 ዓ.ም (ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በከተማዉ በሚገኙ ከ4 ሺህ በላይ ብሎኮች ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የምዘና ተግባር ያለበትን ደረጃ የሚገመግም መድረክ ዛሬ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የቢሮው የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ጥበቡ እና የየክፍለ ከተማዉ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የምዘና ቡድኑ ወደ ስራ ከተሰማራበት ጊዜ ጀምሮ የመረጃ አሰባሰብ እና የብሎኮችን ነባራዊ ሁኔታ የመለየት ስራው ምን ላይ እንደሚገኝ ግምገማ ተደርጎ ተግባሩ ጥሩ ፍጥነት ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፤በየብሎኩ የሚገኘው የሰላም ሰራዊት አደረጃጀትና የማህበረሰብ አቀፍ ውይይቶች በሰላም ግንባታ ላይ እያመጡ ያለው ለውጥ በዝርዝር ታይቷል።
በምዘናው ሂደት ያጋጠሙ ጥቃቅን ክፍተቶች የተለዩ ሲሆን፣ በቀሪ ቀናት ስራውን በጥራትና በታማኝነት ለማጠናቀቅ የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በመድረኩ አቶ ፍስሃ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምዘናው ከተማዋን ከሁከትና ብጥብጥ የጸዳች ለማድረግና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ አስተባባሪዎች ስራውን በተቀመጠው መስፈርት መሰረት በፍጥነት ጥራት ባለዉ መንገድ በተቀመጠዉ የጊዜ ሠሌዳ እንዲያጠናቅቁ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ የ2018 በጀት አመት የተከለሰ እቅድ በዘርፉ ቡድን መሪ አቶ ልቅናዉ ታሪኩ አማካኝነት በሰነድ መልክ ለአስተባባሪዎቹ ቀርቦ ዉይይት ተደርጓል።