የተቀናጀ ስራ በመሰራቱ ምክንያት ጨለማን ተገን ተደርገዉ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መቀነሳቸዉን ተገለፀ።
የተቀናጀ ስራ በመሰራቱ ምክንያት ጨለማን ተገን ተደርገዉ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መቀነሳቸዉን ተገለፀ።
****
ታህሳስ 17/2018 ዓ.ም (ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
በዛሬዉ እለት የአዲስ አበባ ከተማ የመብራት ማስበራት፣ የሲሲቲቪ ካሜራ ገጠማ፣ የሞዴል ፓሊስ ሴንተሪ ግንባታ እና የተቀናጀ የፀጥታ ሀይሎች ስምሪት አረጋጋጭ ኮሚቴ በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ሞዴል ብሎኮችን በመጎብኘት አፈፃፀሙን ገመገመ።
በጉብኝቱና ጉብኝቱን ተከትሎ በተደረገዉ ግምገማ በህዝብ ባለቤትነት ከጨለማ ወደ ብርሀን የተቀየሩ የውስጥ ለውስጥ ብሎኮች እና ቀጠናዎች፣ ለረጅም ጊዜ ሳይበሩ የነበሩ የመንገድ ዳር ፓሎች ጠግኖ እንዲበሩ የማድረግ ፣ ሞዴል የፓሊስ ሴንተሪዎች የመፍጠርና የፀጥታ ስራዉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን እየተዘረጉ ያሉ የሲሲቲቪ ካሜራዎች የከተማዋን ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ለቅሚያና ንጥቂያ መነሻ የሆኑና ለወንጀል የሚዳርጉ የዉስጥ ለዉስጥ ጨለማ ስፍራዎችን በህብረተሰቡ ባለቤትነትና በመንግስት መሪነት አካባቢያቸው ብርሃናማ እንዲሆኑ ለማድረግ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን፤ቢሮዉ በተለያዩ ዙሮች ከማእከል አስከ ወረዳ ያሉ አመራሮችን ባሳተፈ መልኩ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ላይ መብራት የማስበራት፣ ሞዴል ማህበረሰብ አቀፍ ፓሊስ ሴንተሪዎች የመፍጠር፣ ካሜራ የመግጠምና የተቀናጀ የፀጥታ ሀይል የማሰማራት ስራ እየሰራ እንደሆነም ኃላፊዋ ገልጸዋል።
ይህ የውስጥ ለውስጥ እና የመንገድ ዳር መብራት የማስበራት ተግባር ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣በዛሬዉ ዕለትም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በመገኘት ከዚህ ቀደም በምሽት ለመንቀሳቀስ ስጋት የሆኑ እና ወንጀል የሚከሰትባቸዉ ቦታዎች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ብርሃናማ የሆኑ ስፍራዎችን ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ በማድረግ አፈፃፀሙን ገምግሟል።
ክብርት የቢሮ ሀላፊዋ የመስክ ምልከታዉን ለማስጀመር ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት፤የመብራት ማስበራት መርሃ ግብሩ ጨለማን በብርሃን የመተካትና በመስክ ምልከታዉ ወቅት አንዱ ክፍለ ከተማ ከሌላዉ ተሞክሮ በመውሰድ ከተማችን አዲስ አበባ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚደረግባት በመሆኗ ወንጀልን በመቀነስ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን እንደሆነ አንስተዉ፤ከተማዋ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የከተማችን ሰላም፣ ጸጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ለወንጀል መንስኤ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት የሚከሰቱ ወንጀሎችን የመቀነስ ስራ ተሰርቷል ሲሉም ገልጸዋል።
ኃላፊዋ አክለዉም ሰላም ወዳዱ ህብረተሰባችን የአከባቢዉን የበር ላይ መብራት ለማብራት ላደረገዉ አስተዋጽኦ በየደረጃው ያለ አመራር ደግሞ ተግባሩን በሀላፊነት ስላስተባበረ አመስግነዉ፤የብሎኪንግ ስራ የወንጀል ምጣኔን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው ከፓሊስ መዋቅር፣ ከበጎ ፈቃድና ህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለስልጣን፣ ከስራ አስኪያጅ፣ ከደንብ ማስከበር ባለስልጣንና ከሌሎች ደጋፊ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ስለሆነ በየብሎኩ በካሜራ የታገዘ ስራ በመስራት ህብረተሰቡም የሰላም ባለቤትነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ በበኩላቸው ያለፉት ጊዜያቶች ከተማችን ከልማት አኳያ ለውጥ ያሳየች ሲሆን የክፍለ ከተማው የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመስራት በርካታ ብሎኮችና ቀጠናዎች ከስጋት ነጻ መሆን እንዲችሉ ብዙ ስራ መሰራቱንና አንዳንድ ብሎኮች ካሜራ እንዲኖራቸው ማድረግ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፀጥታ አጠባበቅ ስራ እንዲኖር በእቅድ ይዘን በመስራት ላይ እንገኛለንም ሲሉ ተናግረዋል።
ቀጣይ ሁሉም ክ/ከተሞች ዕቅዳቸውን መከለስ እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ማህበረሰቡን በማሳተፍ
ሞዴል የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ሴንተሪዎች ግንባታ በየብሎኩ መስራት፣ መሠረተ ልማት ስርቆት እንዳይፈጸም ጥብቅ ስምሪት መስጠት፣ስታንዳርዱን የጠበቀ ካሜራ ማስገጠም፣ ሞዴል ፓሊስ ሴንተሪዎች መፍጠር፣ የተቀናጀ የመደበኛና የአጋዥ የፀጥታ ሀይሎች ስምሪት መስጠት የሚል የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በመድረኩ ላይ ከከተማ እስከ ክ/ከተማ ያሉ የሰላምና ፀጥታ፣ የስራ አስኪያጅ፣ የህብረተሰብ ተሳትፎና እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ፣ የአዲስ አበባ መብራት አገልግሎት፣ የፓሊስ እና የደንብ ማስከበር መዋቅር አመራሮችና ዳሬክተሮች እንዲሁም የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝቷል።
#በ8882 አጭር የነፃ ስልክ መስመራችን ማንኛውንም ጥቆማና መረጃዎች ያድርሱን ለተጨማሪ መረጃ ዌብሳይታችንን ይጎብኙ http://www.aaps.gov.et/