ቢሮዉ የከተማችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የተሰሩ ስራዎችና የቢሮ የሪፎርም ስራ መሰረት ያደረገ የግምገማ መድረክ አካሄደ።
ቢሮዉ የከተማችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የተሰሩ ስራዎችና የቢሮ የሪፎርም ስራ መሰረት ያደረገ የግምገማ መድረክ አካሄደ።
****
ህዳር 15/2018 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በተያዘው 2018 በጀት አመት በጥቅምት ወር የተሰሩ ስራዎችንና የሪፎርም ተግባራት ላይ ከማእከል አስከ ወረዳ ያሉ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች በተቋም ግንባታ እና አገልግሎት አሰጣጣቸዉ ምን እንደሚመስል ለመቃኘት በተካሄደዉ የመስክ ምልከታ ዙሪያ የግምገማ መድረክ አካሄደ።
ለዉይይቱ መነሻ የሚሆን ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤በሪፖርቱም በጥቅምት ወር የተግባር አፈጻጸም የነበረዉን ጥንካሬና ድክመት እንዲሁም በመስክ ምልከታ ወቅት የተገኙ ግኝቶችን በጥንካሬ እና በድክመት የተስተዋሉ ተግዳሮቶች ተዳሰዉበት ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫን በማመላከት ፤በቢሮዉ የእቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ገብሬ አማካኝነት ለዉይይት ቀርቧል።
መድረኩን የመሩት ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊና አቶ ተስፋዬ ደንድር የቢሮዉ ምክትል የቢሮ ሀላፊና የጸጥታና ኦፕሬሽን ዘርፍ ሀላፊ ናቸዉ።
ክብርት የቢሮ ሀላፊዋ የሰላምና ጸጥታ አመራሮች ከመደበኛ ስራዎችን ጎን ለጎን ህብረተሰቡን እያሳተፍንና የሰላም ባለቤትነቱን በመጨመር የሰላም እሴት ግንባታ ስራዎች፣በከተማዉ የወንጀል መቀነስ ስራ፣ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ የጸጥታ መደፍረስ እንቅስቃሴ መግታትና በበዓላት ወቅት የሚስተዋለውን የጸጥታ ስምሪት በመደበኛ ጊዜያትም በመተግበር መዲናዋ ሰላሟ የተረጋገጠ ከተማ መሆኗን በተጨባጭ እንዲረጋገጥ ማድረግ ይገባል በማለት ውይይቱን በመሩበት ወቅት አንስተዋል።
ሀላፊዋ አክለውም ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎችን በማንሳት በከተማዉ የወንጀል ምጣኔን ከመቀነስ አንጻር ጨለማን ተገን በማድረግ በከተማው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመቀነስ ምቹ መደላድል ለመፍጠር የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ማእከላት 24 ሰዓት ክፍት ሆነዉ ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ በቅንጅት መስራት፣በመንገድ ዳር መብራት የታየዉን ስኬት ዉስጥ ለዉስጥም ነዋሪዉ ጉዳቱን ተገንዝቦ እንዲተገብር በማህረሰብ አቀፍ ዉይይት ማስገንዘብ እንደሚገባ አዉስተዉ፤በየ ክፍለ ከተማዉ የመከላከያ ሰራዊት ምልመላ ያለበትን ሁኔታና የሪፎርም ተግባራት ያለበትን ሁኔታም ከአመራሩ ጋር የገመገሙ ሲሆን፤የ11ዱም ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ሀላፊዎች እንደየ ነባራዊ ሁኔታቸዉ ባቀረቡት ሪፓርት ዙሪያ ሀላፊዋ ማብራሪያና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ።
አቶ ተስፋዬ ደንድር በበኩላቸው የከተማችን የጸጥታና ደህንነት አባላትና አመራሮች ሌት ተቀን በተጠንቀቅ በመቆማቸው ከተማችን ሰላማዊና ደህንነቷ የተረጋገጠች መሆን ችላለች በማለት፤ምቹ የስራ ቦታ መፍጠር የሚቻለዉና የተቻለዉም የሪፎርም ስራ በመተግበሩ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታዉሰዋል።ምክትል ቢሮ ሀላፊዉ አያይዘውም በሰላም እሴት ግንባታ፣ከመከላከያ ምልመላ፣ከወንጀል መከላከልና ከሰላም ሰራዊት ስምሪት ጋር ተያይዞ ከአመራሮቹ በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መድረኩ የ11ዱም ክፍለ ከተማና የየወረዳዉ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ሀላፊዎች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን በቀረበዉ ሪፖርትና በሰላም ግንባታ ሂደት የሚተገበሩ ስራዎችን ታሳቢ በማድረግ በክብርት ሀላፊዋ በተነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተው፤ በጥልቀትና በስፋት ስራዎችን በመገምገም የማጠቃለያ ሃሳብ ተሰጥቶበት ግምገማዊ መድረኩ ተጠናቋል።