ቅንጅታዊ አሰራር
የከተማችንን ፀጥታ ለማስጠበቅ የቅንጅታዊ ስራዎቻችን ማጠናከረ አለበን ተባለ።
ህዳር 6/2018 ዓ.ም (ሰ.ፀ.አስ.ቢሮ)
*****
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ከተለያዩ የፀጥታ አደረጃጀት አመራሮች ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ውይይት አካሄደ።
በውይይቱም ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ም/ል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ጥበቡ ሲሆኑ፣ በንግግራቸውም ባለፉት የተከበሩ የአደባባይ በዓላትና ኩነቶች ያለምንም የፀጥታ ችግር በዓሉ እንዲካሄድ ላደረጉ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበው፣የዛሬው መድረክ በርካታ ትላልቅ ተልዕኮዎችን ወስደን ስራዎቻችን ሳንዘናጋ ለማስቀጠልና እንዲሁም በከተማችን ያሉ የፀጥታ ጉዳዮች ለማስጠበቅ እና እየታዩ ያሉ ዝርፍያዎችን በመከታተልና መረጃ በመስጠት የመከላከል፣ችግሮችን በመነጋገር በመወያየት ለመፍታት፣ጸጉረ ለውጦችን አንዳንድ ቦታዎች እየታዩና እየተያዙ ያሉትን አደጋ ሳያስከተሉ የፀጥታ አካላት ጥብቅ ክትትልና የቅድመ መከላከል እንዲሁም ቅንጅታዊ ስራዎቻችን አጠናክረን ለማስቀጠል የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል።
ለውይይቱም መነሻ የሚሆን ሰነድ ያቀረቡት የዘርፉ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ልቅናው ታሪኩ ሲሆኑ፣በገለፃቸውም ወቅት በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ፣ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ዙሪያ፣ከንግድና ኢኮኖሚ አሻጥር ጋር በተያያዘ፣ ከትራንስፖርትና ታክሲ ተርሚናሎች፣የአከባቢን ሰላም ለማስጠበቅ የሰላም ሰራዊት ሚና በተመለከተና ሌሎችም በሰነዱ አብራርተዋል።
ሰነዱን መነሻ በማድረግ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሃሳቦች እና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ሀላፊው አክለውም ከተሳታፊዎቹ የተነሱ አስተያየቶች ለቀጣይ ስራዎቻችን ገንቢና ግብዓት እንደሚሆን ጠቅሰው፣ማህበረሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆኑ ማወያየት በየቀጠናቹ የሚፈጠሩ ችግሮችን መለየት፣ህብረተሰቡን ማሳታፍ፣ቅንጅታዊ አሰራርን ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት መስራት እንዳለባቸውና የፀጥታ ስጋት የሆኑ ቦታዎችን ማወቅና መቀነስ፣አዋኪ ድርጋቶች የሚካሄዱበት ቦታዎች የወንጀል መሸሸግያና መፈጸምያ እንዳይሆኑ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው በማጠቃለያቸው አሳስበዋል።
በውይይቱም ላይ አቶ ፍስሐ ጥበቡ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ም/ቢሮ ኃላፊ፣የአዲስ አበባ ከተማ የፖሊስ አመራሮች፣የማዕከልና የክ/ከተሞች ዳይሬክተር፣አስተባባሪ፣ቡድን መሪዎች፣በከተማው የተደራጁ የሰላም ሰራዊት፣ጫኝና አውራጅ ተገኝተዋል።