የከተማችን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ግምገማ
የከተማችን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ እንዲሁም የደንብ ጥሰት መከላከልና መቆጣጠር አፈፃፀም ተገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫ ተቀመጠ፡፡
ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም
***
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮና የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የከተማችንን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ እንዲሁም የደንብ ጥሰት መከላከልና መቆጣጠር አፈፃፀምን በዛሬው ዕለት በጋራ በመሆን ገመገሙ፡፡
በከተማችን የሰላምና ደህንነት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች፣ አዝማሚያዎች፣ የደንብ ጥሰት መከላከልና መቆጣጠር በተመለከተ እና አጠቃላይ መሰራት ያለባቸው ስራዎች በጋራና በተናጥል እንዲሰሩ ቀድሞ አቅጣጫ መሰጠቱን አንስተው፣ ተግባራቱ አሁን ያሉበትን ደረጃ ሁለቱም ተቋማት በጋራ በመሆን ገምግመዋል።
ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር እና የአዲስ አበባ ከተማ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ም/ል ስራ አስኪያጅ አቶ ከፍያለው ታደሰ ሲሆኑ፣ ውይይቱን በመሩበት ወቅት፣ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምንድነው የሚለውንና ተግባራቶች፣ አዝማሚያዎችን ያየንበት ትልቅ ማሳያና ማንቂያ ግምገማ እንደሆነ ገልጸው፣ የምሽት ንግዶችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ በየቦታው የሚታዩ ከልመናዎች ጋር በተያያዘ በደንብ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትል እንዲደረግ፣ በየአከባቢዎች ነገሮች መልክ ቀይረው የሚመጡበት ሁኔታዎችን፣ ጉዳዮችን ትኩረት መስጠት፣ ጽንፈኛ ሀይሎችን በተመለከተ አሁን ላይ እየተስፋፉ ስለሆነ የመከታተል የመቆጣጠርና መረጃዎችን የመሰብሰብ ጠንካራ የሆነ እርምጃዎችን መውሰድ፣ፎርጅዶችንና የልጆች መጥፋት፣የቡድን ፀቦችን ልዩ ትኩረት እንደሚፈልጉና የቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሆኑ አስቀምጠዋል።
የሁለቱም ተቋም የክ/ከተሞች ጽ/ቤት ኃላፊዎችና አመራሮች፣ አመራሩ ለሰላምና ደህንነት ለደንብ ጥሰቶች ትኩረት ሰጥተው፣ በየክ/ከተማው ያሉ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም፣ መረጃዎችን በመሰብሰብ በከተማው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎችን ኦፕሬሽን በማድረግ የህግ ተጠያቂና ምርመራ እየተደረገባቸው እንዳለም ገልጸዋል።
በተለይም ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ተያይዞ የውስጥ ችግሮቻቸውን ወደ ውጭ በማውጣት ወደ ብሔር የመውሰድ፣ ጽንፈኛን የመደበቅ አዝማምያዎች በስልጣንና በጥቅም ያለመግባባት ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፣በደንብ ትኩረት ተሰጥቶት ክትትል መደረግ እንዳለበትም በግምገማው አንስተዋል።
የሁለቱም ተቋም ም/ል ኃላፊዎች ከሁሉ ክ/ከተሞች በቀረበው ሪፖርትና ግምገማዎች አኳያ፣ቀጣይ በቅንጅት በመሆን የክ/ከተሞች ባሕሪ የተጠናከረ ስራዎች መሰራት እንዳለበትና በቂ ዕውቀት ላይ ተመርኩዞ፣ሁኔታን አውቆ፣በቤተ ዕምነቶችና ት/ቤቶች በተለይም አሁን ያለንበትን ሁኔታ አውቆ መስራት እንዳለብን የሚያመላክት ግምገማ እንደሆነና የወጣትና ብሔራዊ በጎ ፈቃድ ላይም የአመራሮች ትኩረት አለማግኘትና በደንብ ተገምግሞ መታየት እንዳለበት ገልጸዋል።
በመጨረሻም የከተማዋን ሰላምና ደህንነቷን ለማስጠበቅ ህብረተሰቡን ማወያየት፣በየብሎኩ የሚደረጉ የቡና ጠጡ ፕሮግራሞችን በማጠናከር ማስቀጥል፣የሰላም ሰራዊት አባላትን ዕለት ተዕለት ማነቃቃት፣የፖለቲካ አመራሩ አቅጣጫ ሰጥቶ ወደስራ የማስገባት ስራና ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ የአከባቢያቸውን ሰላም ማስጠበቅ፣መረጃዎችን ለፀጥታ አካላት በመስጠት ወንጀሎችን መቀነስ እንዳለባቸው አመራሮች እንደ መፍትሔ አስቀምጠዋል።
በግምገማው የማዕከል ም/ል አመራሮች፣የክ/ከተሞች የሰላምና ፀጥታ አስተዳደርና የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የክ/ከተሞችና የወረዳዎች አመራሮችና ጽ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።