የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የመስቀል ደመራ በዓል የማጠቃለያ መርሀ-ግብር አካሄደ
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመተባበር የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የማጠቃለያ መርሀ-ግብር አካሄደ።
**
መስከረም 12/2017 ዓ.ም(አዲስአበባ)
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመተባበር የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የማጠቃለያ መርሀ-ግብር በአድዋ ሙዚየም አካሄደ።
ዉይይቱን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ሲሆኑ፤የመስቀል ደመራ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገበ ከኢትዮጵያ አልፎ
የአለምን ትኩረት የሳበ ብዙሃኑን በሚያንፀባርቅ መልኩ ኢትዮጵያን ከፍ ካደረጉ የአደባባይ በዓላት አንዱ እንደ ሆነ ጠቅሰዉ፤ከተለያዩ ክልሎች የሚሳተፉ ሰዎች የእርስ በርስ መስተጋብር የሚፈጥር በመሆኑ ለሀገር ግንባ ትልቅ ሚና የሚጫወት እና የጋራ ማንነትን የሚያጎለብት በዓል ስለመሆኑ ገልጸዋል።በዓሉ ለቱሪዝም ማበልጸጊያም ጭምር እንደሆነ የጠቀሱት መጋቢ ታምራት፤ለበዓሉ ስጋት ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ ጉዳዮችን በመለየት በታላቅ ድምቀት የሚከበር በመሆኑ የመጨረሻ አቅጣጫ የሚሰጥበት ዉይይት ነዉ ሲሉም የመርሃግብሩን አላማ ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ፣የሀዲያ፣የስልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የአዲስአበባ የሀይማኖት ተቋማት የቦርድ ሰብሳቢና የሲኖዶስ አባል የሆኑት ብጹዕ አቡነ ህርያቆስ ዉይይቱ በይፋ እንዲከፈት ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤የመስቀል በዓልን በምን መልኩ ሰላማዊ አድርገን ማክበር አለብን የሚለዉን ለመወያየት የተፈጠረ የዉይይት መርሃግብር ነዉ በማለት፤መስቀሉን ስናከብር በመስቀል ላይ የተሰቀለዉን ክርስቶስን የድንግል ማሪያምን ልጅ በማሰብ ስለሆነ በመላው አለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን፣ኤርትራውያንና ሌሎችም መስቀል የሠላም ምልክት መሆኑን በማብሰር በሠላምና በአንድነት እንድናከብር ሲሉ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤በሀገራችን የአብሮነት እና የመቻቻል ካስማ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስረን ገመድ የማይበጠስ ስለመሆኑ የመስከረም ወር አንዱ ማሳያ ነዉ በማለት፤የለዉጡ መንግስታችን ጠቃሚ ሀይማኖታዊ በዓላት ትዉፊታቸዉን ጠብቀው እንዲከበሩ የበኩሉን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛልም ሲሉ ገልጸዋል።
ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ አክለዉም፤መስቀል የብርሃን ምልክት በመሆኑ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊያን የብዙሃነት ማሳያ በአለም አደባባይ ይመሠክራል ብለዉ የ2018 መስቀል ልዩ የሚያደርገው ህዳሴ ግድባችን በተመረቀበት ማግስት የባዳን የቀረርቶና የሽለላ በመግታት በራስ አቅም የማልማት ህያዉ ምስክርና የማይደፈር ሀገራዊ ቁመና ላይ ባለንበት ወቅት መሆኑ ነዉ ካሉ በኃላ፤
የተለያዩ አህጉራዊና ሀገራዊ ሀይማኖታዊ በዓላት እሴቶቻቸዉን ጠብቀዉ እንዲያልፉ ሠላማችንን አደጋ ላይ ለመጣል የሀይማኖት ካባ የለበሱ ለጊዜያዊ ጥቅም የሚንቀሳቀሱ ስለማይጠፉ ሰላም ከሌለ ሀይማኖታዊ በዓላት ማክበር አይታሰብምና አብረን መስራታችንን አጠናክረን የደመራ በዓል ሀይማኖታዊ ትዉፊቱን ብቻ ጠብቀን፤የኮሪደር ልማት ዉጤቶችንም በጋራ በመጠበቅ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ አባታዊ ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ በማለት አሳስበዋል።
ለዉይይቱ መነሻ የሚሆን ከመስቀል ደመራ ጋር የተያያዘ ጽሁፍ የብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ፕሮቶኮል እና ልዩ ጸኃፊ በሆኑት ቀሲስ አብይ ዘለቀ አማካኝነት ቀርቦ ሰፋ ያለ ጥያቄና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተሰንዝሯል።
የዉይይት መድረኩን የመሩት፤ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ የሃዲያና የስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ፣ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ዋና ፀኃፊ
ሲሆኑ ከተወያያዮች በተነሱት ጥያቄና አስተያየቶች ዙሪያ ከአወያዮች ምላሽ የተሠጠ ሲሆን በ2018 የመስቀል በዓል ሁሉም አድባራት ያልተገቡ ከበዓሉ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የብሔርና የሃይማኖት ይዘት ያላቸዉ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖር ጌቱ አሳስበዋል ።በቀጣይም በትኩረት መሠራት ያሉባቸው ጉዳዮች በአቅጣጫ መልክ ከመድረኩ መሪዎች ተሠጥቷል።
በዉይይቱ መድረክ ላይም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የሀይማኖት እና ሰላም እሴት ግንባታ ዘርፍ ሀላፊና ም/የቢሮ ሀላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ፣ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገ/መድህን ንጉሴ የአዲስ አበባ ሃገረስብከት ስራ አስኪያጅ፣ መልአከ ህይወት አባወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊ፣የ11ዱም ክፍለ ከተማ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ ከከተማ እስከ ወረዳ ያሉ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።