የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ከንዑሳን ኮሚቴ ጋር ዉይይት አካሄደ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በቀጣይ ሳምንት የሚካሄደውን የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ከንዑሳን ኮሚቴ ጋር ዉይይት አካሄደ።
*
መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በመስከረም ወር የሚካሄዱ ትላልቅ ሐይማኖታዊና ባህላዊ ቱባ በዓላት ፍጹም ሰላማዊ ሆነዉ እንዲጠናቀቁ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። የተግባሩ አንድ አካል በማድረግም በዛሬዉ እለት መስከረም 09/2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክቶ በዓሉን በባለቤትነት ከምትመራዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር ቢሮዉ ዉይይት አካሂዷል።
ዉይይቱን የመሩት ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ሲሆኑ፤ በቅርስነት የተመዘገቡ ትላልቅ ሐይማኖታዊም ሆኑ የትውፊታችን አካል የሆኑ ባህላዊ የአደባባይ በዓላት ሲኖሩ መንግስት የሚሰራዉ ስራ እንዳለ ሆኖ አጠቃላይ ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ የመስቀል ደመራ በዓልን በባለቤትነት ከምትመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር ዉይይት በማድረግ በዓሉ የየትኛውም አካል እኩይ ተግባር መጠቀሚያ ሳይሆን ሐይማኖታዊ እሴቱንና ትዉፊቱን ጠብቆ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በማለም የዛሬው ዉይይት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ሀላፊዋ አክለዉም ቢሮዉ ከመስከረም 01 ጀምሮ በእቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን በማዉሳት፤ ሰላም ላይ ማተኮሩ አዋጭ ብቻ ሳይሆን ከተማችን ለሌሎችም ጭምር ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ህብረብሔራዊ አንድነትን የሚያሳይና አዲስ አበባን ተምሳሌት ሊያደርግ የሚችል የሰላም ግንባታ ላይ በመስራት በዓሉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ነዉ ብለዋል።
በዉይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ሀላፊና የሀይማኖትና ሰላም እሴት ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ እና የቤተክርስቲያኒቱ የመስቀል ደመራ በዓል ዝግጅት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተሳትፈዋል።
ኮሚቴዎቹ በበኩላቸው ከከተማ አስተዳደሩ ለሚደረገዉ የሰላምና ድጋፍ ብሎም ትብብር አመስግነዉ፤ የአደባባይ በዓላት ለሀገርና ለአለምም ጭምር የሚሰጠዉን ጠቀሜታ በማሰብ ሰፊ ትኩረት ተሠጥቶ መስራቱ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ በመጠቆም ቤተ ክርስቲያኗ በቅድመ ዝግጅት እየሠራች ያለዉን ስራ ኮሚቴዎቹ እንደየ ሀላፊነታቸው ተግባሩ እየተመራ ያለበትን አግባብ በዉይይቱ ወቅት አቅርበዋል።
በበዓሉ ወቅት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በዝርዝር ያነሱት ኮሚቴዎቹ በበዓላቱ ላይ አቅመ ደካሞች ጭምር የሚሳተፉ በመሆኑ የመድረክ ዝግጅት እና በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ከወዲሁ መስራት እንደሚያሻ አመላክተዋል።
የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ እንደተናገሩት ታላቁ የአደባባይ በዓል የሆነዉ የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያውያን የተበረከተ ሀይማኖታዊ ይዘቱና ባህላዊ ትውፊቱ ተሰናስነው የሚከበርበት በዓል በመሆኑ ከመንፈሳዊነት ወጣ ያሉ የፓለቲካ ይዘት ያለው ነገር እንዳይኖር ቢሮው የሚችለዉን ስራ እየሠራ እንደሚገኝ በመግለፅ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ያሳየዉን የአደባባይ በዓላት ፍፁም ሰላማዊ የማድረግ ጉዳይ ላይ ምእመኑን ጭምር በማስገንዘብ ቤተክሪስቲያንቱ ከቢሮዉ ጋር በቅንጅት በመስራት የበዓሉ አከባበር ፋይዳነቱ ለቤተክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገርን ገጽታ ግንባታ ጭምር ያለዉ ሚና የጎላ ስለሆነ ፍፁም ሰላማዊነቱ ላይ በጋራ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው መስቀል የሠላም፣ የይቅርታና የአንድነት በዓል የሆነ እና ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች በአለም አደባባይ በድምቀት የሚያሳዩበት ፤በዩኔስኮም ጭምር ክትትል የሚደረግበት በዓል እንደሆነ ጠቅሰዉ፤ በዓሉ ላይ ሌላ የፓለቲካ አጀንዳ የሚያራምድ አካል በዓሉን እንዳያዉክ ቤተክርስቲያኗ የማትነቃነቅ ተገፍታ የማትወድቅ መሆኗን ሊያሳይ የሚችል ተግባር መፈጸም እንደሚገባ ገልጸዉ፤ በዓሉ ለቱሪስት ፍሰቱ ያለዉን ፋይዳ ለኢኮኖሚው እድገት ያለዉን በጎ ተጽእኖና ሀገር እየሠራች ካለዉ ልማት ጋር በማስተሳሰር ሁሉም ሠላሙ ላይ በቅንጅት መስራት እንዳለበት አብራርተዋል።
በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ከንዑሳን ኮሚቴዎች የተነሱ ሀሳብና አስተያየቶች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሠጡ ሲሆን፤ በቀሪ ጊዜያት መከናወን ባሉባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ሰጥተዉ ዉይይቱ ተጠናቋል።