የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ማስጀመር መርሃ-ግብር ተከናውኗል።
"ቢሮው በ90 ቀናት እቅዱ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የአቅመ ደካሞችን ቤት ያድሳል።"
ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ
ሰኔ/28/2017 (አአ ሰፀአ ቢሮ)
********
በ90 ቀናት እቅድ ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ ስራችንን በማጠናከር በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የአቅመ ደካማ ቤቶችን እናድሳለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አስታወቁ።
በዛሬው ዕለት በአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ክብርት ቢሮ ኃላፊዋና የክፍለ ከተማ አመራሮች ነዋሪዎች ብሔራዊ የበጎ ፈቃደኞች በተገኙበት የ90 ቀናት እቅድ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ማስጀመር መርሃ-ግብር ተከናውኗል።
የበጎ ፈቃድ መርሃግብሩን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንደተናገሩት በሰው ተኮር ስራዎች መንግስት የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ አብሮነትን መረዳዳትን ባህል ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ቢሮ ኃላፊዋ አክለውም የ13ኛ ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ወጣቶች አብሮነት ለማሳደግ አንድነትን ለማጽናት ለሀገር ተረካቢ ወጣቶች አርያ በመሆን ለምትሰሩት ተግባር ልትመሰገኑ ይገባል ካሉ በኋላ በ11ዱም ክፍለ ከተማደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተን እናስረክባለን ብለዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ወገሴ በበኩላቸው በመረዳዳትና በመተጋገዝ ድህነትን እናሸንፋለን ብለዋል።
አቶ ወልዴ አክለውም አቅመ ደካሞችን ችግር በመረዳት ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትና የግል ባለሀብቶች ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታሁን አበራ በዚህን ወቅት እንዳሉት በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ደራሽ በመሆን በትብብር ከሰራን ሀገራችንን ለማሻገር ትልቅ እርምጃ ይሆናል ብለዋል።
አቶ ጌታሁን ጨምረው እንዳሉት በ90 ቀናት የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በመተግበር እቅዳችንን ለማሳካት በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።